ጌታችን በሮማውያን እጅ ዕርቃኑን በተሰቀለበት ዕለት ከቀኑ በስድስት ሰዓት ላይ ታላቋ የእሳት ኳስ ብርሃናዊቷ ፀሐይ ድንገት ጨለመች፤ ጨረቃም ደም መሰለች፤ ከዋክብትም ረገፉ (ጨለሙ)። በነቢዩ ሚልክያስ ‹‹ስሜን ለምትፈሩ ለእናንተ የጽድቅ ፀሐይ ትወጣላችኋለች፤ ፈውስም በክንፎችዋ ውስጥ ይሆናል›› ተብሎ በትንቢት የተነገረለት እውነተኛው ፀሐይ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ እጆቹን እንደ ክንፍ በዘረጋ ጊዜ በእውነተኛው ፀሐይ ፊት ማብራት ያልተቻላት ፀሐይ በድንገት ጨለመች። (ሚል. ፬፥፪) በመዞር ምክንያት የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ የሌለበት፣ ለሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ክርስቶስ በመስቀል ላይ እንደተሰቀለ ባየች ጊዜ ታናሽዋ ፀሐይ ብርሃንዋን ከለከለች።

ማንነቱን ያልተረዱት አይሁድ ዕርቃኑን ሰቅለው እያዩ ሊዘብቱበት ሲቆሙ ፍጥረታቱ ግን አምላካቸው ተሰቅሎ አይተው መቋቋም ተሳናቸው፤ ስለ ጌታችን ሥቃይ ምድርን በኀዘን አጨለሟት፣ ስለ ጌታችን ደም መፍሰስ ጨረቃ ደም መሰለች፤ ሰዎች በፈጣሪ ፊት ስላሳዩት ድፍረት የሰዎች መገኛ የሆነችው ምድር ተንቀጠቀጠች፣ ሰውነቱ በግርፋት መሰንጠቁን አይተው ዓለታትም ተሰነጣጠቁ። ‹‹ፍጥረታት ሁሉ በሥቃዩ አብረውት ተሠቃዩ፤ ሲሰቀል እንዳታየው ፀሐይ ፊትዋን ሸሸገች። ከእርሱ ጋር አብራ ልትሞት ብርሃንዋን አጠፋች፤ ለሦስት ሰዓታት ጨለማ ከሆነ በኋላ ግን መልሳ አበራች፤ ይህም በሦስተኛው ቀን እንደሚነሣ  ስትመስክር ነው›› ይላል ቅዱስ ኤፍሬም።

              የሰማይ ብርሃናት የመጨለማቸው ምክንያት የጌታችንን ዕርቃኑን እነርሱ በብርሃናቸው አይተው ለሌላው ላለማሳየት ነው። አባ ጊዮርጊስ ‹ፀሐይ ጸልመ፤ ወወርኅ ደመ ኮነ፤ ወከዋክብት ወድቁ ፍጡነ፤ ከመ ኢይርአዩ ዕርቃኖ ለዘአልበሶሙ ብርሃነ › ‹ፀሐይ ጨለመ፤ ጨረቃም ደም ሆነ፤ ከዋክብትም ፈጥነው ወደቁ፤ ብርሃንን ያለበሳቸውን አምላክ ዕርቃኑን እንዳያዩ› በማለት እንደዘመረው በብርሃን ያስጌጣቸውን የፈጣሪን ዕርቃኑን ላለማየት (ማሰብ የማይችሉት ፍጥረታት በብርሃናት ላይ በተሾሙ መላእክት እጅ) ብርሃናቸውን ሠወሩ።

ጻድቁ ኖኅ የወይን ጠጅን ጠጥቶ በሰከረና ዕርቃኑን በሆነበት ዕለት ልጁ ካም ዕርቃኑን እያየ ሲዘብትበት ሴምና ያፌት የተባሉት ልጆቹ ግን የአባታቸውን ዕርቃን ሸፍነው ነበር። (ዘፍ. ፱፥፳፩‐፳፫) እንደ ኖኅ በጠጅ ሳይሆን በሰው ልጅ ፍቅር ሰክሮ ዕርቃኑን በመስቀል ላይ የተሰቀለውን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስንም አይሁድ እንደ ካም ሲዘብቱበት፤ ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት ግን እንደ ሴምና ያፌት ዕርቃኑን ሸፈኑለት።    

              ነቢያቱ አስቀድመው ስለዚያ የቀትር ጨለማ ትንቢቶችን ተናግረው ነበር። በነቢዩ ዘካርያስ ‹‹አንድ ቀን ይሆናል፤ እርሱም በእግዚአብሔር ዘንድ የታወቀ ይሆናል፤ ቀንም አይሆንም ሌሊትም አይሆንም፤ ሲመሽም ብርሃን ይሆናል›› ተብሎ ተጽፎ ነበር። (ዘካ. ፲፬፥፯) በእርግጥም አንድ ቀን የተባለው ዕለተ ዓርብ ነው። ‹ቀንም አይሆንም ሌሊትም አይሆንም› ያሰኘው የሦስት ሰዓታቱ ጨለማ ነው። ቀን እንዳይባል ጨልሟል፤ ሌሊት እንዳይባል ደግሞ ከቀኑ ስድስት ሰዓት ነው። ሲመሽ ብርሃን ይሆናል የተባለው ደግሞ ከዘጠኝ ሰዓት በኋላ ብርሃኑ ስለተመለሰ ነው።

ከደቂቀ ነቢያት በአንዱ በአሞጽ አንደበት ደግሞ እግዚአብሔር እንዲህ ተናግሮ ነበር ፡- ‹‹በዚያ ቀን ፀሐይ በቀትር እንድትገባ አደርጋለሁ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ በብርሃንም ቀን ምድሩን አጨልማለሁ፤ ዓመት በዓላችሁንም ወደ ልቅሶ ዝማሬያችሁንም ወደ ዋይታ እለውጣለሁ፤ እንደ አንድያ ልጅም ልቅሶ ፍጻሜውንም እንደ መራራ ቀን አደርገዋለሁ›› (አሞ. ፰፥፱‐፲) ይህም ስለ ዕለተ ዓርብ የተነገረ ነበር። የዓመት በዓላቸው ፋሲካ በሚከበርበት ዕለት ፀሐይ ጨለመች፤ የኢየሩሳሌም ሴቶች ልቅሶም የትንቢቱ መፈጸሚያ ሆነ እግዚአብሔር ይህንን የተፈጥሮ ምላሽ የፈቀደው አይሁድ አምላክነቱን ተረድተው ከክፉ መንገዳቸው እንዲመለሱ ጥሪ ለማድረግ ነበር። ለቁጣ ቢሆን ኖሮ ሁሉንም መሬት ተሰንጥቃ እንድትውጣቸው ለማድረግ ይቻለው ነበር። እርሱ ግን ‹‹ፀሐይን አጨለመ፤ ገዳዮቹን ግን አልተቀየመም›› ‹‹ፀሐይኒ አጽለመ፤ ወቀታሊያነ ኢተቀየመ›› (ግብረ ሕማማት ዘዓርብ ፮ ሰዓት) የሚያሳዝነው ግን የሰቀሉት አይሁድን ‹ተፈጥሮ እንኳን› አላስተማራቸውም፤ ‹‹ሰማያውያን እርሱን እንዳያዩ ፊቱን ሸፈኑ ምድራውያን ግን ምራቃቸውን ይተፉበት ነበር›› መሬት ፈርታ ስትንቀጠቀጥ አይሁድ ግን አልተንቀጠቀጡም፤ ‹‹ዓለት ተሰነጠቀ፤ የዐመፀኞቹ ልብ ግን አልተመለሰም›› ልባቸው ከዓለት ይልቅ የደነደነ ነበር። በዚያች በዕለተ ዓርብ ከነበረው መነዋወጥ የተነሣ ዓለም ልታልፍ ትችል ነበር። ቸርነቱ የበዛው አምላክ ‹‹ምድርን ያለ ጊዜዋ እንዳታልፍ አጸናት፤ ደሙን በምድር ላይ አፈሰሰ፤ ከኅልፈት ጠበቃት በእርስዋ ያለውንም ሁሉ ጠበቀ››

በዕለተ ዓርብ ከተፈጸሙት ተአምራት ሁሉ ግን እጅግ አስደናቂው ተአምር የሰው ልጅ መዳኑ ነው። ከፀሐይ መጨለምና ከጨረቃ ደም መምሰል በላይ የእኛ የጨለመ ማንነታችንን ብሩሕ ማድረጉ፣ ከቤተ መቅደስ መጋረጃ መቀቀድ በላይ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የነበረው የጥል ግድግዳ መፍረሱ፣ ከሙታን ከመቃብር መውጣት በላይ የሰው ልጆች ከሲኦል መውጣቱ፣ የክርስቶስ የደሙ ጠብታ ዓለምን ከኃጢአት ማጠቧ እጅግ አስደናቂዎቹ የመስቀል ላይ ተአምራት ናቸው። ቅዱስ ያሬድ ‹‹ምድር በክርስቶስ ደም ታጥባ ፋሲካን ታደርጋለች›› (ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ ተሐጺባ በደመ ክርስቶስ) በማለት ስለዚህ ተአምር ዘምሯል።

በሦስቱ ሰዓታት ውስጥ ስለነበረው ስለ ሰማይ ብርሃናት ሁኔታ በወንጌላት የተጻፈው የፀሐይ መጨለም ብቻ ሲሆን ስለ ጨረቃ ደም መሆንና ስለ ከዋክብት መጨለም በወንጌላቱ ውስጥ አልተመዘገበም። ነቢያቱና ሐዋርያቱ ግን ዕለተ ዓርብን ከዕለተ ምጽዓት በሚያስተባብሩ ትንቢቶቻቸውና ትምህርቶቻቸው የጨረቃና የከዋክብትን ነገርም መዝግበውልናል።

‹‹ፀሐይና ጨረቃ ጨልመዋል፤ ከዋክብትም ብርሃናቸውን ሰውረዋል፤ እግዚአብሔርም በጽዮን ሆኖ ድምፁን ከፍ አድርጎ ይጮኻል›› (ኢዮ. ፫፥፲፭)

‹‹ምድሪቱ በፊታቸው ትናወጣለች፤ ሰማያትም ይንቀጠቀጣሉ፤ ፀሐይና ጨረቃም ይጨልማሉ፤ ከዋክብትም ብርሃናቸውን ይሰውራሉ›› (ኢዮ. ፪፥፲)

‹‹የሰማይ ከዋክብትና ሠራዊቱ ብርሃናቸውን አይሠጡም፤ ፀሐይም በወጣች ጊዜ ትጨልማለች፤ ጨረቃም በብርሃኑ አያበራም›› (ኢሳ. ፲፫፥፲)

    ቅዱስ ጴጥሮስ በሦስት ሺህ ሰዎች ፊት ባስተማረበት በዕለተ ጰራቅሊጦስም የነቢዩ ኢዮኤልን ትንቢት ሲጠቅስ ‹‹ታላቅ የሆነ የተሰማም የጌታ ቀን ሳይመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣሉ፤ የጌታን ስም የሚጠራም ይድናል›› በማለት ተናግሯል። (ሐዋ. ፪፥፳‐፳፩) ይህ ትንቢት በዕለተ ዓርብ በፀሐይና ጨረቃ የተፈጸመ ሲሆን ‹የጌታን ስም የሚጠራ ይድናል› የሚለው ቃል ደግሞ ከጌታ ቀኝ በተሰቀለው ወንበዴ መዳን ተፈጽሟል፡፡ ነቢዩ ኢዮኤል ስለ ዕለተ ምጽዓት የተናገረውን ይህን ትንቢት ቅዱስ ጴጥሮስ ጠቅሶ ማስተማሩም በዚያ ለተሰበሰቡት አይሁድ በዕለተ ዓርብ የተፈጸሙትን ተአምራት በማስታወስ ባለማመናቸው ከጸኑ ሊመጣባቸው የሚችለውን እንዲገምቱ ሲያመለክት እንደሆነ ሊቃውንት ያብራራሉ።

በዕለተ ዓርብ የተከሰተውን የፀሐይን መጨለም በየዘመናቱ የተካነ ጥበብ ነበር። የግሪካውያን ፍልስፍና እጅግ የመጠቀውና ለብዙ የሳይንስ ዘርፎች ስም አውጪ የሆነው አዳዲስ አሳቦች ተከብረው የሚሰሙበት እንዲህ ያለ ሥፍራ የውይይት ቦታ ከጥንት ስለነበረ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ሲሰብክ ሰምተው ወዲህ ሲያመጡት በአርዮስፋጎስ ከተሰበሰቡት ሊቃውንት መካከል የፍርድ ቤት ዳኛ የነበረው ዲዮናስዮስም ተገኝቶ ነበረ። በዚያን ቀን እነዚያ ፈላስፎች ከጳውሎስ ጋር ብዙ ክርክሮችን አድርገው ግማሾቹ ሲያፌዙበት ግማሾቹ ግን በክርስቶስ አመኑ።

 በሐዋርያት ሥራ ላይ እንደተጻፈው ቅዱስ ዲዮናስዮስ ካመኑት ጥቂት ሰዎች አንዱ መሆን የቻለ ሲሆን ‹በክርስቶስ አምላክነት አምኜያለሁ› ያለውም መዝግቦ ያስቀመጠው ፀሐይ የጨለመችበት ዕለት መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ የተሰቀለበት ዕለተ ዓርብ መሆኑን ከቅዱስ ጳውሎስ ጠይቆ በማረጋገጡ ነበር። የፀሐይ መጨለም ዓለም አቀፍ ክስተት በመሆኑ ምክንያት ቤተ ክርስቲያናችን የብዙ ድርሰቶች ጸሐፊ የሆነውን ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ዲዮናስዮስን ዘአርዮስፋጎስን አገኘች። አስደናቂዋ ፀሐይ ለዲዮናስዮስ ጨልማ  አበራለችለት!!    

ሕማማት ገፅ 400

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ