Let us remember the poor, and not forget kindness to strangers; above all, let us love God with all our soul, and might, and strength and our neighbor as ourselves.”

Timket Celebration

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን

ክቡራንና ክቡራት ይህንን መንፈሳዊና የጥምቀት ዓመታዊ በዓል ለማክበር የታደማችሁ የልዑል እግዚአብሔር ቤተሰቦች የእናታችን የቅድስተ ቅዱሳን የንጽሕት ድንግል ማርያም የአሥራት ልጆች በቅድሚያ እንኴን ለ 2010 ዓ/ም ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት በሰላም አደረሳችሁ።

“ሖረ ኢየሱስ አምገሊላ ኀበ ዮሐንስ ከመ ያጥምቆ በፈለገ ዮርዳኖስ ” ማቴ 313

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ በዓለ ጥምቀት ከበዓለ ልደት ቀጥሎ የሚከበር ዓቢይ በዓል ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ይህንን በዓል ታቦታተ ሕጉን ይዛ ከቅጽረ ቤተክርስቲያን ወጥታ በዝማሬ እና በእልልታ በሜዳ በወንዝ ዳር የምታከብረው ያለምክንያት አይደለም። ከላይ በርእሱ እንደተገለጸው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ ይጠመቅ ዘንድ ከገሊላ አውራጃ ከናዝሬት ከተማ ወደ ይሁዳ አውራጃ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ መጥቶ መጠመቁን አብነት መሠረት በማድረግ ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ለምን ተጠመቀ ?

ይህ ጥያቄ ብዙ ምሥጢር ያለው ቢሆንም ባጭሩ ለመግለጽ ክብር ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሃጢያት ኖሮበት ሳይሆን፤

  • በነቢያት የተነገረውን ትንቢት ለመፈጸም
  • ውሃውን ለመቀደስ
  • የአዳምን እዳ ለመደምሰስ
  • ለጥምቀት ሃይልን ለማሰጠት
  • ለእኛም አርአያና ምሣሌ ለመሆን በዮሐንስ እጅ በፈለገ ዮርዳኖስ ተጠመቀ

1ኛ፤ ከዘመናት በፊት በነቢዮ ዳዊት የተነገረው ትንቢት፤ ይህም ትንቢት “ባሕርኒ ርእየት ወጎየት ወዮ ርዳኖስኒ ገብአ ድኀሬሁ አድባር አንፈርአጹ ከመ ሐራጊት ” ባህር አየች ሸሸችም ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ ተራሮችም እንደ ኮርማዎች ዘለሉ። መዝ 113/114 3-6 በማለት

2ኛ፤ እንደዚሁም በዮሐንስ እጅ መጠመቁ “ወናሁ አነ እፌኑ መልዓክየ ዘይጸይህ ፍኖትየ በቅድመ ገጽከ ” መንገዱን ለማዘጋጀት ቃል ኪዳኑን ለማወጅ እግዚአብሔር አስቀድሞ መልዕክተኛውን ይልካል። ትን ሚል 3፤ 1-3 በማለት የተነገርው ትንቢት ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ በፈለገ ዮርዳኖስ ተጠምቆ ሲወጣ “ወናሁ ተርኀወ ሰማይ ወርእየ መንፈሰ እግዚአብሔር እንዘ ይወርድ ከመ ርግብ ወይወርድ ላእሌሁ ”  ሰማይ ተከፍቶ መንፈስ ቅዱስ በአምሳለ ርግብ ወርዶ በራሱ ሲቀመጥ መጥምቁ ዮሐንስ አየ እንደዚሁም “ መጽአ ቃል እምደመና ዘይብል ዝንቱ ውእቱ ውልድየ ዘአፈቅር ወሎቱ ስምእዎ ” ለተዋህዶ የመረጥሁት በእርሱ ህልው ሆኜ ልመለክበት የወደድሁት ልጄ ይህ ነው። እርሱን ስሙት የሚል ቃል ከወደ ሰማይ ተሰማ ወንጌላውያኑም በዚህ ምሥጢረ ሥላሴን በግልጽ አስተምረውናል። አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ ተጠምቆ ከውሃው ሲወጣ የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል በራሱ ላይ ሲያርፍ የባሕርይ አባቱ አብም የወደድሁት ልጄ ይህ ነው በማለት በእርሱ ህልው መሆኑን መስክሯል።

በዚይም የባሕርይ አምላክነቱን እና የባሕርይ ልጅነቱን ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ አስመስክሮበታል። ምሥጢረ ሥጋዊ ከሦስቱ አካላት ሁለተኛው አካል ቃለ እግዚአብሔር ወልድ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ የመገለጡ አምላክ ሰው ሰው አምላክ የመሆኑ ምሥጢር ነው “ቃል ሥጋ ኮነ ወሃደረ ላእሌነ ” ቃል ሥጋ ሆነ በእኛም አደረ ዮሐ 1፤14 በማለት ሐዋርያው እንዳስተማረን ስለዚህ በምሣሌና በምሥጢር የተገለጸውን ካማጤን ጋር የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ አንድነት እና ሦስትነት የታወቀበት ዕለት መሆኑን ተገንዝበን እምነታችንን አጽንተን እንድንይዝ ያስተምረናል። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል አከባበር ዋናው ምሥጢር ይህ ነው። እግዚአብሔር አምላካችን በዓሉን የተቀደሰ በዓል ያድርግልን! ለሀገራችን ለቤተ ክርስቲያናችን ለሕዝባችን ሰላምን ፍቅርን አንድነትን ያድለን።

ወስብሐት እግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን

Share:

You May Also Like

The term “descended from the heavens” holds significance in the context of fasting to commemorate the help of God. This...
Members of churches belonging to the Ethiopian Orthodox Tewahedo Church from Boston and its surrounding cities gathered for Timket (Epiphany),...
Full Kidan and Kidase services streaming via YouTube and Facebook on May 10th, 2010 Sermon was delivered, Gospel Luke 24...