በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን
የደብረ መ/ቅ/ገብርኤል ወልደታ ለማርያም ቤ/ክ አመሠራረት ባጭሩ በእግዚአብሔር ቸርነትና ቅዱስ ፈቃድ ታህሳሥ 5 ቀን 2007 ዓ/ም (12/11/2014) ከ30 ያላነሱ ምእመናን በተገኙበት መልክአ ሥዕልና ፀሎተ ኪዳን ተደርሶ በፀሎተ ምህላ ተጀመረ::
ታህሳሥ 11 ቀን 2007 ዓ/ም (12/20/2014 ) በሀ/ስ/ሊ/ጳጳስ በብፁእ አቡነ ዘካርያስ ፀሎተ ቡራኬ ከ130 በላይ የሚሆኑ ምእመናን በተገኙበት ቅዳሴ ቤቱ ተከበረ:: በዚሁ ዕለትም የደብሩ ሥያሜ “ደብረ መንክራት ቅዱስ ገብርኤል” በመባል ተስይሟል::በዚሁ ዕለት ምእመናን ለ7 ወራት የሚሆን የህንፃ ኪራይ ለመሸፈን ቃል ገቡ::
ከዛን ጊዜ ጀምሮ የደብሩ አግልግሎት እየሰፋና እየተጠናረ በመምጣቱ በአብሣሪው ቅዱስ ገብርኤል ቤ/ክርስቲያን የተበሣሪዋ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታቦት ቢገባ መልካም መሆኑ በብፁእ አባታችን አቡነ ዘካርያስ ፈቃድ ስላገኘ ሐምሌ 19 ቀን 2007 ዓ/ም (08/27/2015 ) የቅ/ገብርኤል ዓመታዊ በዓለ ንግሥ ከ300 እስከ 400 የሚሆኑ ምዕመናን በተገኙበት በሚከበርበት ወቅት በብፁእ አቡነ ዘካርያስ ፀሎተ ቡራኬ የእመቤታችን ታቦት ከመንበሩ ተቀምጧል:: በዚህም ምክንያት የደብሩ መጠሪያ “ደብረ መንክራት ቅዱስ ገብርኤል ወልደታ ለማርያም” ተብሎ ተሰይሟል :: ቤተክርስቲያኒቷ ከምታሳየው የመንፈሳዊ አገልግሎት ስፋት የተነሣ ካህናትንና ምዕመናን መሳብ በመቻሏ ዛሬ የደረሰንበት ልዕልና ላይ እንገኛለን።ለዚህም የንስሃ ልጆቻቸውን የቤተክርስቲያንን ዶግማና ቀኖና በማስተማር በመንፈሳዊ አገልግሎታቸው ደከመኝና ሰለቸኝ ሳይሉ በተጋት በማገልገል ወደ ቅድስት ቤ/ክ እንዲሰበሰቡ በማድረግ ረገድ ካህናቱን ሳናመሰግን አናልፍም።እንዲሁም በዚህ አገልግሎት ተሳትፎ ለተባበሩን ዲያቆናት እና ክርስቲያናዊ ስነምግባር ላልተለያቸው ምዕመናን ከፍ ያለ ምስጋናችንን እናቀርባለን።
ስለዚህም ደብሩ 5 ካህናት 7 ዲያቆናት በድምሩ 11 አገልጋዮች እና ከ100-200 የሚድርሱ ምእመናንንም ያሉት ሲሆን በአሁኑ ሰአትም ተተኪ ትውልድ ለማፍራትም በርካታ ሕፃናትንም በማስተማር ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላድትቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን ::